Tuesday 2 July 2013

እየሩሳሌም


            “እየሩሳሌምን በልባችሁ አስቡ” ‹‹.ኤር 51÷51››
ነቢዩ ኤርምያስ ከክርስቶስ ልደት በፊት በ539 ዓ/ዓለም ገደማ ስለኢየሩሳሌም ነፃ መውጣት እና ስለ ባቢሎን መፍረስ የተናገረው ነው፡፡ ፍፃሜውም በኢየሩሳሌም ስለሚፈጸመው ነገረድኅነት እና ከክርስቲያኖች ልብ የማትጠፋ ሀገር ስለመሆኗ የሚያመለክት ነው፡፡
እስራኤል
አምላካችን ልዑል እግዚአብሔር ለይስሐቅ ልጅ ለያዕቆብ የሰጠው ስያሜ ነው፣ ካልባረከኝ አልለቅምህ ብሎ ነበርና “ከእግዚአብሔር ጋር ይታገላል ያሸንፋል” ሲል እስራኤል አለው፡፡ ዘፍ. 32÷22 በኋላም የያዕቆብ ልጆች የተጠሩበት እና ከሰሎሞን በኋላ ዐሥሩ ነገዶች ያቋቋሙት የሰሜናዊው ግዛት (መንግሥት) ስያሜ ሆኗል፡፡ ዘፍ 49÷7 ዘዳ 14÷39 1ኛ ነገ.12÷16
 በአዲስ ኪዳን የክርስቶስ ተከታዮች እስራኤል ዘነፍስ ተብለዋል ሮሜ. 9 ገላ. 3÷6 ሮሜ. 4÷12
እየሩሳሌም
ኢየሩሳሌም ማለት መሠረት ሠላም፣ ሀገረ ሠላም፣ የሠላም ምልክት…. ማለት ነው፡፡ ስትጠራም የእግዚአብሔር ከተማ፣ ቅድስት ከተማ፣ የዳዊት ከተማ ተብላ በቅዱሳት መጻሕፍት ተጠቅሳለች ንጉሠ ሰላም የተባለው የጌታችን ምሳሌ ሆኖ የሚነገረው መልከፄዴክ እንደመሠረታት ይነገራል፡፡ ዘፍ. 14÷ ነህ. 11÷1 የአበ ብዙኃን አብርሃም የልጆቹ፣ የበርካታ ነቢያት ሀገራቸው ፣ ታላቁ ንጉሥ ቅዱስ ዳዊትም ከኢያቡሳውያን ማርኮ ከተማው ያደረጋት በመሆኗ የነቢያት ትንቢት ፍፃሜ አግኝቶ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከልደት እስከ ዕርገት የኖረባት፣ ሐዋርያት የተጠሩባት፣ ነገረድኅነት የተፈፀመባት በመሆኗ በእውነትም ቅድስት ሀገር ናት፣ በማዕከለ ኢየሩሳሌም ጽርሐጽዮን የሰሎሞን ቤተመቅደስ፣ ከጲላጦስ አደባባይ እስከ ቀራንዮ መከራ መስቀል የተቀበለባቸው ቦታዎች ይገኛሉ፡፡ 



4 አቅጣጫዎች የሚገኙ ቦታዎች
በምድረ እስራኤል በ4ቱም አቅጣጫዎች በርካታ ቦታዎች የሚገኙ ሲሆን በዚህ መጠነኛ ጽሑፍ ግን በመጽሐፍ ቅዱስ በስፋት የተገለፁትን ቦታዎች ለማመልከትና የአሁኑን ይዞታቸውን ለመጠቆም ብቻ ይሞከራል፣ ከአቅጣጫዎቹ መሠረት/መካከል/ የሚደረጉት ማዕከለ ምድረ ቀራንዮ የሚገኝባትን ኢየሩሳሌም ነው፡፡
ሰሜን
. የገሊላ ባህር- ገሊላ የአካባቢው እና የባህሩ መጠሪያ ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ገሊላ፣ ጌንሴሬጥ፣ ጥብርያዶስ ተብሏል፡፡ ማቴ 41÷18፣ማር.1÷14፣ ዮሐ 20÷1 ሞቃታማ እና ከሙት ባህር ቀጥሎ በዓለማችን ዝቅተኛ ከሚባሉ ቦታዎች አንዱ ነው፡፡ የሜድትራኒያን ባህር ካለበት የመሬት ደረጃ 212 ሜትር ዝቅ ያለ ነው፡፡ ከኢየሩሳሌም በ100 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ በባህረ ገሊላ ደቀመዛሙርቱን የጠራበት፣ በባህሩ ላይ መራመድ፣ ከትንሣኤ በኋላም የተገለጠበት እና በርካታ ተአምራት የተፈፀሙበት ቦታ ነው፡፡ ማር.15÷40፣ ሉቃ 8÷2፣ ዮሐ. 21÷1፣ ማቴ. 8÷23
በጥብርያዶስ ከተማ በአሁኑ ጊዜ የክርስቲያን፣ የሙስሊም እና የአይሁድ ተከታዮች ይገኛሉ፡፡
. ቅፍርናሆም፡- ቅፍርናሆም ዛሬ የመታሰቢያ ታሪኳ ብቻ ቢገኝም በዚሁ ባህር ዳርቻ እንደነበረች ይታመናል፡፡ ወንጌላዊው ማቴዎስ የተጠራባት፣ የኢያኤሮስን ልጅ ከሞት ያስነሳበት በቤተመቅደስም ሕሙማንን የፈወሰባት ቦታ ናት ማር 2 ማቴ. 9÷9-8 (8÷16) በዘመኑ የነበሩትም ታአምራቱን አይተው ስላለመኑ ከጠፉ ከተሞች አንዷ ሆናለች፡፡
. ቃና ዘገሊላ- ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእመቤታችን አማላጅነት ውሃውን ወደ ወይን ጠጅ የለወጠበት ቦታ ስትሆን በናዝሬት በስተሰሜን አቅጣጫ የምትገኝ ትንሽ መንደር ናት ዮሐ. 2÷2-11
. ናዝሬት- እመቤታችንን ቅዱስ ገብርኤል ያበሠራት በናዝሬት ነው ጌታችንም ለአረጋዊ ዮሴፍ እየታዘዘ 30 ዓመት ኖሮበታል፡፡ ሉቃ. 1÷26-28 ማር. 1÷9 ሐዋርያው ናትናኤል ከናዝሬት የተገኘ ነው፡፡ ዮ. 1÷46 (7÷52)
እመቤታችን በቤተዮሴፍ ውሃ ትቀዳበት የነበረው ቦታም የሚገኝ ሲሆን ዛሬ የግሪኮች ይዞታ በመሆኑ ቤተክርስቲያን ሠርተውበታል፡፡ ቅዱስ ገብርኤል ያበሠረበት ቦታ ላይም የላቲኖች ቤተክርስቲያን ይገኛል፡፡
. ደብረታቦር- ከኢየሩሳሌም በስተሰሜን ከናዝሬት በምሥራቅ አቅጣጫ 9 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ ነቢይቱ ዲቦራ በባለቅ መሪነት ሲሳራን ድል ያደረገችበት በአዲስ ኪዳን ደግሞ ብርሃነ መለኮቱን የገለጠበት ቦታ ነው መሳ. 4÷6 ማቴ 17÷1 መዝ. 88÷12 ማር. 9÷2 ሉቃ.9÷28
ዐጸዶች የተከበበ፣ ተራራማ፣ በጣም በልምላሜ የተሸፈነ ከእስራኤል ቦታዎች ልዩ የሆነ ቦታ ነው ከተራራው ላይ ሆኖ በርቀት የአርሞንኤም ተራራ፣ ጥብርያዶስስ የኤስድሮስ ሸለቆ ይታያሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት ግሪኮችና ላቲኖች ቤተክርስቲያን ሠርተውበታል፡፡
. ቤቴል፡- የእግዚአብሔር ቤት ማለት ሲሆን፣ አብርሃም ድንኳኑን የተከለባት፣ ያዕቆብ ከምድር እስከ ሰማይ የሚደርስ መሰላል ያየባትልዩ ቦታ ናት፡፡ ካፍ 12÷8 (28÷10-22) መሳ 20÷26 2ኛ ነገ. 2÷2-23
. ሰማርያ- ሰማርያ ከክርስቶስ ልደት በፊት በ800 ዓመት ዓለም አምረ በተባለው ንጉሥ መመሥረቷ ይነገራል፡፡ በርካታ የእስራኤል ነገሥታት ተቀብረውባታል፡፡  አንድ የነበረው የእስራኤል መንግሥት በሮብአምና በኢዮርብአም ከኹለት ከተከፈለ በኋላ ዐሥሩ ነገድ በኢዮርብአም ንጉሥነት በሰሜኑ መንግሥት ሆኑ፣ ኹለቱ ነገድ ይሁዳና ብንያም ደግሞ ኢየሩሳሌምን ይዘው ኖሩ፡፡ የሰሜኑ የእስራኤል መንግሥት መናገሻ ከተማዎች የመጀመሪያዋ ሴኬም፣ ከዚያም ጵንኤል፣ ቀጥሎም ቲዝረህ ከተዘዋረ በኋላ በመጨረሻ ሰማርያ ሆናለች፡፡ 1ኛ ነገ/6÷24 1ኛ ነገ 22÷1-22 2ኛ ነገ. 6÷6-18 ጠንቋይ የነበረው ሲምን ቅዱስ ፊልጶስም ያስተማረበት ቦታ ስለመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ ያስረዳል፡፡ ሐዋ 8÷5 (9÷13)

ደቡብ
. ቤተልሔም- በዕብራይስጥ የእንጀራ ቤት ማለት ነው፡፡ ከኢየሩሳሌም በስተደቡብ የፍልስጤም ግዛት ስትሆን ከኢየሩሳሌም 8 ኪሎ ሜ. ርቀት ላይ ትገኛለች፡፡ በዘመነ ብሉይ ራሔል የተቀበረችበት የኑኃሚን ሀገር፣ ሩትና ቦዔዝ የኖሩበት ስለመሆኗ ተጽፏል፡፡ ዘፍ. 35÷16 1፡(4) ነቢዩ ዳዊትም የተወለደባት እንደሆነ ይታወቃል፡፡
ቀድሞ ኤፍራታ ትባልም ነበር፡፡ ጌታችን የተወለደባት፣ እረኞች የመልአኩን ብሥራት የሰሙባት፣ ሰብዐሰገል የሰገዱበት ቅድስት ቦታ ሉቃ. 2÷14 ማቴ 2÷16 ንግሥት ዕሌኒ በ326 ዓ.ም ታላቅ ቤተመቅደስ አሠርታለች ይህም እስከዛሬ ይገኛል፡፡
. የፊሊጲስ ምንጭ፡- ሐዋርያው ፊልጶስ ኢትዮጵያዊውን ጀንደረባ ያጠመቀበት ቦታ ምንጩ በዐረብኛ ዓይነዲርዋ ይባላል ምንጩ በድንጋይ ታጥሮ ቢገኝም በቦታው ግን ቤተክርስቲያን አልተሠራም፡፡ ሐዋ 8÷26-39
ሐ. ኬብሮን፡- ቀድሞ የመማጸኛ ከተሞች እንዲሆኑ ከተደረጉ አንዷ ነበረች፡፡ ኢያ 21÷13 አሁን ኤል ካሊል ተብላ የዐረቦች ከተማ ናት፡፡ ከኢየሩሳሌም ምድር ከፍተኛዋ (ከፍታ ያላት) ቦታ ስትሆን ከባህር ወለል በላይ 930 ሜትር ትሆናለች በመጽሐፍ ቅዱስ በተለያዩ ስሞች እና ታሪኮች ተጠቅሳለች፡፡ ዘፍ 23÷19 ኢያ 14÷15  ዘኁ.13÷22 ኢያ. 14÷13 2ኛ. ሳሙ.5÷1-5 በይበልጥም የአበው /አብርሃም፣ ሣራ፣ ይስሐቅ…መቃብር የሚገኝበት መሆኑ ይታወቃል፡፡
መ. መምህሬ- መምሬ በተባለ አምራዊ ስም የተሰየመ ቦታ ሲሆን አብርሃም የሠፈረበት ቦታ ነው፡፡ ዘፍ. 14÷12 (12÷18) እንደዚሁም አብርሃም እግዚአብሔርን በእንግድነት የተቀበለበት መሆኑ በስፋት ይታወቃ ዘፍ. 18÷1 በኬብሮን አቅራቢያ 3 ኪ.ሜ ወደ ቂርያት በሚወስደው መንገድ ሲገኝ የመምሬ አድባር ዛፎች ቅሬት ይገኝበታል፡፡
ምስራቅ
ሀ. ኢያሪኮ፡- ከኢየሩሳሌም በስተምሥራቅ 5 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ በዮርዳኖስ ወንዝ አቅራቢ ትገኛለች፡፡ ትርጓሜዋ የጨረቃ ከተማ፣ የመልካም መዓዛ ቦታ ማለት ነው፡፡ እሥራኤል ምድረ ርስትን ሲካፈሉ ለብንያም ደረሰች፡፡ ኢሳ 18÷21 ሙት ባህር ሲያዋስናት ከባህር ወለል በታች 258 ሜትር ዝቅ ብላ የምትገኝ በረሃማ ናት ዘፍ. 32÷49 በርካታ ታሪኮች ተፈጽመውባታል፤ ዘፍ 26÷1-4 (22÷1) ዘላ. 34÷ኢ 5÷13(6) 2ኛ ነገ.2
      በአዲስ ኪዳን መጥመቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ በዮርዳኖስ ሲያጠምቅ ቦታው በኢያሪኮ ከተማ ጠርዝ ላይ መሆኑ እና የዘኬዎስ ሀገር መሆኑ ተጠቃሽ ነው፡፡ ማቴ.3÷13፣ ሉቃ 19÷1-8 እንደዚሁም ብዙ ሕሙማን የፈወሰበት ቦታ ነው፡፡ ማቴ 20÷29 ማር. 10÷46፣ ሉቃ. 18÷35

ለ. ገዳመ ቆሮንቶስ፡- ጌታችን ዐርባ መዓልትና ሌሊት የጾመበት ቦታ ከኢያሪኮ በስተሰሜን ተራራ ቦታ 3 ኪ.ሜ ላይ ይገኛል፡፡ አሁን የግሪኮች ይዞታ ሲሆን “ኮራንታ” በላቲን 40 ማለት ስለሆነ ቦታው በተለምዶ ገዳመ ቆሮንቶስ ተብሏል፡፡ ማቴ 4÷1-4፡፡
ሐ. የደርዳኖስ ወንዝ፡- በመጽሐፍ ቅዱስ በብሉይ 175 በሐዲስ 15 ጊዜያት የተጠቀሰ ወንዝ ነው፡፡ ቃሉ ዕብራይስጥ ሲሆን ወራጅ ማለት ነው፡፡ ከአርሞንኤም ተራራዎች ተነሥቶ እስከ ሙትባህር ይወርዳል፡፡ በብሉይ ከተጠቀሱትም ጥቂቶቹ ዘፍ 13÷22 ኢያ.3÷15 2ኛ ነገሥ. 6 (6÷4) 2ኛ ነገ. 5÷14 እንደሚታወቀው ጌታችን ጥምቀትን ሊመሰርት፣ ዕዳችንን ሊደመስስ በዮርዳኖስ ተጠመቀ ማቴ. 3 ሉቃ 3
መ. የጨው ባህር፡- በመጽሐፍ ቅዱስ ጨው ባህር፣ የአራባህ ባህር፣ ምሥራቃዊ ባህር ሲባል በተለይም ደግሞ ሙት ባህር ይባላል ዘፍ. 14÷13 ዘዳ. 3÷17 2ኛ ዜና 20 ኢያ 3÷16 በተጨማሪም በታሪክ ባህረ ሎጥ የሰዶምና ገሞራ ባህር የዞግር ባህር ይባላል፡፡
በዓለማችን በጣም ዝቅተኛው እና ሕይወት ያለው ነገር የማይኖርበት ባሕር ነው፡፡ የባህሩ ዳርቻ ከመሬት ወለል በታች  423 ሜትር ነው፡፡ በምሥራቅ ጆርዳንን፣ በምዕራብ እስራኤልን ሲያዋስን ስፋቱ 18 ኪ.ሜ. ይደርሳል፡፡ ዋና ገባሩም የዮርዳኖስ ወንዝ ነው፡፡
ነቢዩ ሕዝቅኤል ባህሩ አንድ ቀን ዓሣ እንደሚገኝበት (እንደሚፈወስ) ትንቢት ተነግሮለታል፡፡ ሕዝ 47÷8
.ቁምራን፡- ዌስት ባንክ አካባቢ የሚገኝ ቦታ ሲሆን ጥንታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅልሎች የተገኙበት ነው ከሙትባህር በስተሰሜን 2 ሴ.ሜ. ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ በይበልጥም ከ1947-1956 ከ800 በላይ ሃይማኖታዊ መጽሐፍት በአብዛኛው ከመጽሐፈ አስቴር በስተቀር የብሉይ መጻሕፍት (ጥቅልሎች) እንደተገኙበት ይነገራል፡፡
. ጌልጌላ፡- የእስራኤል ልጆች ዮርዳኖስን ተሻግረው ለመጀመሪያ ጊዜ የሠፈሩት ጌልጌላ ነው፡፡ ኢያ. 4÷19፣ ኢያ 5÷1-15 የተለያዩ ድርጊቶችም ተፈጽመውበታል፡፡ ኢያ 5÷9፣ 1ኛ ሳሙ. 13÷8 2ኛ ነገ.ሠ 4÷38
. ደብረዘይት፡- የወይራ ዛፍ የበዛበት ተራራ ማለት ሲሆን ከኢየሩሳሌም በምሥራቅ ይገኛል፡፡ በዘመነ ብሉይ ብዙ ታሪክ ሲኖረው በይበልጥ ዳዊት ከአቤሰሎም የሸሸበት ቦታ ስለመሆኑ በስፋት ተጽፏል፡፡ 2ኛ ሳሙ. 14÷30
    መድኃኒታን ኢየሱስ ክርስቶስ ያድርበት የነበረ ዋሻ ይገኛል፡፡ አቡነ ዘበሰማያት፣ ነገረ ምጽአቱን ያስተማረበት ቦታ መሆኑም ይታወቃል፡፡ ማቴ 6(24) በተነሣ በዐርባ ቀኑ ያረገው በደብረዘይት ሲሆን ለፍርድ ሲመጣ እግሮቹ የሚቆሙበት መሆኑ የታመነ ነው፡፡ ሉቃ 24÷5 ዘካ. 12÷4
. ቤተፋጌ- የበለስ ቤት ማለት ሲሆን ደብረዘይት አጠገብ ይገኛል፡፡ ወደ ቤተመቅደስ ለመግባት ጉዞ የጀመረበት እና አህያይቱና ውርንጭላዋ የተገኙበት ቦታ ነው፡፡ ሉቃ 19÷28 ማቴ 21
. ጌቴሴማኒ (አፀደ ሐዎል)- ለምለም የአትክልት ቦታ ማለት ነው፡፡ ጌታችን በጸሎተ ሐሙስ የጸለየበት፣ የእመቤታችን ወላጆች ቦታ ነበርና መቃብሯ ያለበት፣ ቅዱስ እስጢፋኖስ የተወገረበት አካባቢ ነው፡፡ የወይራ ዛፎች አስከ ካሬ በቦታው ይገኛሉ፡፡ የላቲን እና የግሪኮች አብያተክርስቲያናት ታንጸውበታል፡፡ ማቴ 26÷41 ዮሐ. 17 ሐዋ. 7
. ጽርሐጽዮን፡- “እስመኅረያ እግዚአብሔር ለጽዮን” ጽዮንን እግዚአብሔር ድንቅ ሥራውን ሊገልጥባት መርጧታል፡፡ የዳዊት ከተማ የነበረች፣ የነገሥታት መቃብር የሚገኝባት፣ የእግዚአብሔር ታቦት በክብር ተቀምጣ የነበረችበት ቦታ ስለመሆኗ በብሉይ ኪዳን ተነግሮላታል፡፡ መዝ. 131 መዝ. 86
   በአዲስ ኪዳን በምሴተ ሐሙስ ጌታችን የሐዋርያትን እግር ያጠበበት፣ ምሥጢረ ቁርባን የመሠረተበት ከትንሣኤው በኋላ በዝግ ቤት ለሐዋርያት የተገለጠበትት በተነሣ በ50 ቀኑ ለሐዋርት መንፈስ ቅዱስ የወረደበት እና እመቤታችን 14 ዓመት ኖራበት በዕረፍቷ ጊዜ የከበረ ሥጋዋ ወደጌቴሴማኒ የወረደችበት ቅድስት ሥፍራ መሆኗን ቅዱሳን መጻሕፍት ይመሠክራሉ፡፡ ማቴ. 26÷26 ዮሐ. 13 ማቴ. 28÷8 ዮሐ. 20 ሐዋ. 2 (ተአምረማርያም እና ስንክሳር)
. ቤተሳይዳ፡- ቤተሣህል ማለት ሲሆን የ38 ዓመት ሕመምተኛው (መጻጉዕ) የተፈወሰበት ቦታ ነው፡፡ ከቀራንዮ አጠገብ ይገኛል፡፡ ዮሐ. 5 ዛሬ የላቲን ካቶሊኮች ቤተክርስቲያን ሠርተውበታል፡፡ የመጠመቂያ ቦታው እና የእርከኑ ፍርስራሽ ይገኛል፡፡
ምዕራብ
. ኤማሁስ፡- ከኢየሩሳሌም 60 ምዕራፍ በአሁኑ 11 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ ትገኛለች፡፡ ጌታችን ለሉቃስና ቀለዮጳ የተገለጠበት ቦታ ነው፡፡ ሉቃ 24÷13-34 የቀለዮጳ ቤትም በዚያ እንደሚገኝ ይነገራል፡፡ ነገር ግን ዛሬ በብዛት በኤማሁስ ስም እየተጎበኘች የምትገኘው ከኢሩሳም 23 ሲ.ሜ ርቀት ላይ ወደ ቴልኢቪቨ ከተማ መንገድ ላይ የምትገኝ በሮማውያን ዘመን አምዋስ ተብላ የተጠራችው  ቦታ ናት፡፡ የቦታው ርቀተ ከወንጌሉ ጋር አለመገጣጠሙ እንዳይረጋገጥ አድርጎታል፡፡ የብዙ አጥኚዎች ማስረጃ እንደሚያመለክተው ቀድሞውን የጠቀስነው በረሀማ በነቢዩ ሳሙኤል መቃብር አጠገብብ የቀለዮጳ የቤቱ ፍርስራሽ የሚገኝበት መሆኑን ነው፡፡
. ቤተሳሚስ- የፀሐይ ቤት ማለት ሲሆን ከኢየሩሳሌም በስተምዕራብ 26 . ላይ የሚገኝ ቦታ ነው፡፡
    በመጽሐፍ ቅዱስ የከነዓናውያን ከተማ ለሌዋውያን የተሰጠ፣ ፍልስጥኤማውያን እንደያዟት…የመሳሰሉ ታሪኮች ተፈጽመውበታል፡፡ ኢያ 21÷16 (15÷10) 1ኛ ሳሙ 6÷91-0 2ኛ ዜና 28÷18
. ዓይነኮርም የመጥምቀ መለኮት ወላጆች የኖሩበት የዘካርያስ እና የኤልሳቤጥ አገር ነው፡፡ አካባቢው ወይናደጋ እና ለምለም ሥፍራ ነው፡፡ ሉቃ 1÷6 ዛሬ በዙሪያዋ የተለያዩ ሀገራት ቤተክርስቲያን ሠርተውበታል፡፡ እመቤታችን እና ኤልሳቤጥ በተገናኙበት ቦታ በተሠራው ቤተክርስቲያን ውስጥ ጸሎተ እግዝእትነ ማርያም በብዙ ቋንቋዎች የእኛም በድንጋይ ላይ በግእዝ ተጽፎ ይታያል፡፡
. ልዳ- በአሁኑ አጠራር ሎድ ይሉታል፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ኤንያን የፈወሰበት ስለመሆኑ በግብረሐዋርያት ሠፍሯል፡፡ ሐዋ. 9÷32 የሰማዕቱ የቅዱስ ጊዮርጊስ መቃብር እና የታሠረበት ሠንሠለት ይገኛል፡፡
. ኤዮጴ- በኢየሩሳሌም በስተምዕራብ ወደቴላቪቭ ሲጓዙ የሚገኝ ትንሽ መንደር (ቦታ) ሲሆን ቅዱስ ጴጥሮስ ጣቢታን ያስነሳበት ቦታ ነው፡፡ እንደዚሁም ሰምዖን የተባለው ቁርበት ፋቂ ይኖርበት ስለነበር ቅዱስ ጴጥሮስ በእርሱ ቤት ተቀምጧል፡፡ ሐዋ. 9÷36 በአሁኑ ጊዜ የካቶሊክ የቅ/ጴጥሮስ ቤተክርስቲያን ይገኝበታል፡፡
.ቀርሜሎስ- ፍሬያማ የአትክልት ቦታ ማለት ነው፡፡ የነቢዩ ኤልያስ መሥዋዕት ያረገበት 450 ካህናተ ጣዖት የተገደሉበት፣ ነቢዩ ኤልሳዕም የኖረበት ቦታ ነበር፡፡ 2 ኛ ነገ. 18÷17 1ኛ. 18÷30 በዛፎች የተከበበ እና ተራራማ ቦታ ነው፡፡ 2ኛ ነገ. 4÷25 

የኢትዮጵያ ገዳማት በኢየሩሳሌም
የኢትዮጵያና የእስራኤል ግንኙነት በዘመነ ብሉይ በንግሥተ ሳባ ወደ ሰሎሞን በመሄዷ የተጀመረ መሆኑ የተረጋገጠ ነው፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሕዝበ ኢትዮጵያ ለበዓል /ሊሠግዱ/ ወደ ኢየሩሳሌም እየተጓዙ ኖረዋል፡፡ በመሆኑም ከዴር ሱልጣን ጀምሮ የኢትዮጵያ ቦታዎች አሏት፡፡
1.    ዴር ሱልጣን፡- ንግሥት ሳባ ከክ.ል በፊት በ1013 ዓመተ ዓለም ገደማ ኢየሩሳሌም ስትሄድ ሠራዊቷን እና ጓዟን ያሳረፈችበት ቦታ ነው፡፡ 1ኛ ነገ. 10፣ 2ኛ ዜና. 9÷1-9 ቀራንዮ (ጎልጎታ) አጠገብ ይገኛል፡፡ በተለያዩ የተንኮል ተግባራት ዋናውን ግብጻውያን የወሰዱት ሲሆን አሁን የአርባዕቱ እንስሳ እና የቅዱስ ሚካኤል ታቦታት የሚገኝበት ጠበብ ያሉ ቤተመቅደሶች እና በጥም ጠባብ የሆኑ የመነኮሳት ማደሪያዎች ይገኙበታል፡፡
2.   ቅዱስ ፊልጶስ፡- የኢትዮጵያ መንበረ ጵጵስና የሚገኝበት ሲሆን የገዳሙ ጽ/ቤት እና ኢትዮጵያዊውን ጀንደረባ ባጠመቀው በቅዱስ ፊልጶስ ስም ቤተክርስቲያን ይገኛል፡፡ በአፄ ዮሐንስ ትእዛዝ መ/ር ወልደሰማዕት በ1883 ዓ.ም የገዙት ቦታ ነው፡፡
3.   ደብረገነት ኪዳነምህረት፡- አሮጌ ከተማ ከሚባለው ውጪ በነቢያት መንገድ አጠገበት ትገኛለች፡፡ የመነኮሳት መኖሪያ የእንግዶች መቀበያ እና አዳራሽ በመግቢያዋ የሚገኝ ሰፋ ያለ ይዞታችን ሲሆን ወደ ገዳሙ የሚወስደው መግቢያ መንገድም “ርሆብ ኢትዮጵያ” ተብሎ ይጠራል፡፡  ቦታው በ1882 ዓ.ም አፄ ዮሐንስ በላኩት ወርቅ የተገዛ ሲሆን ሕንጻውን ያስፈጸሙት በ1885 ዓ.ም. አፄ ምኒልክ ናቸው፡፡
ከላይ የተጠቀሱት ይዞታቸው በኢሩሳሌም ከተማ የሚገኙ ናቸው፡፡
4.   አቡነ ተክለሃይማኖት/አልአዛር/- በኢየሩሳሌም በስተምሥራቅ 12ሺህ ሜትር ካሬ ስፋት ለው የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ይዞታ ሲገኝ በጽድቁ አቡነ ተክለሃይማኖት ስም ቤ/ክ ታንጿል፡፡  የኢትዮጵያን መካነ መቃብር በዚህ ይገኛል፡፡ አፄ ኃ/ሥላሴ ያስገዙት ቦታ ሲሆን በአቡነ ፊልጶስ ጊዜ በ1953 ዓ.ም. ተመሠረተ፡፡
5.   ቅድስት ሥላሴ፡- በዮርዳኖስ ወንዝ አጠገብ ከሩብ ጋሻ የማያንስ ቦታ ሲኖር የቅድስት ሥላሴ ቤተክርስቲያን ተሰርቷል፡፡ ነገር ግን በአረቦችና በእሥራኤል ጦርነት ምክንያት በአካባቢ ሰው ሊኖር ባለመቻሉ ታቦቱም መነኮሳቱም ተዘዋውረው በኢያሪኮ ይኖራሉ፡፡ ቤተክርስቲያኑ በ1925 ዓ.ም. በእቴጌ መነን የጠተሠራ እንደነበረ ይነገራል፡፡
6.   ቅዱስ ገብርኤል፡- በኢያሪኮ ከተማ ለብዙ ጊዜያት የአትክልት ቦታ ሆኖ የቆየው የኢትዮጵያ ይዞታ የቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ይገኝበታል፡፡ ቦታውን የሠጡት ወ/ሮ አማረች ዋለሉ በኋላ እማሆይ አማረች የተባሉ እናት በ1928 ዓ.ም ገዝተውት ለገዳሙ ሰጥተዋል፡፡
7.   ቤተልሔም፡- በምድረ ፍልስጥኤም ጌታችን ከተወለደበት ቦታ አጠገብ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ይገኛል፡፡ ቦታው ልዑል ራስ ካሣና ልዑል መኮንን ወደ ኢየሩሳሌም ሲመጡ ያስገዙት ነው፡፡
ስለ ቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም ማወቅ መጽሐፍ ቅዱስን በስፋት ለመገንዘብ ያስችላል፡፡ ነገረድኅነት የተፈጸመባትን ቦታ ማሰብም መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ሰው ልጆች የፈጸመውን ፍቅሩን ዘወትር ከልብ ለማሰብ ይረዳል፡፡ በቅድስት ሀገር የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ይዞታ እንዳላት ስናስተውል ዳግም የእግዚአብሔርን ቸርነት፣ የአባታችንን ትጋት እንድናወድስ ያደርጋል፡፡ በመሆኑም ለመጻፍ፣ ለመናር፣ ትውፊታችንን ለመጠበቅ ማወቅ ይቀደማልና የበለጠ ስለ ቅድስት ሀገር እና ስለ ይዞታዎቻችን በስፋት እንድናውቅ ዘወትር ኢየሩሳሌምን በልባችን እንድናስብ መልእክታችን ነው፡፡
ብረሳሽ ቀኜ ትርሳኝመዝ. 136÷5

                                                          ቀሲስ ፋሲል ታደሰ
የታ/ነ/በዓታ ለማርያም የዳግማዊ ምኒልክ መታሰቢያ
 መንፈሳዊ ት/ቤት የሐዲሳት ደቀመዝሙር




No comments:

Post a Comment